Numbers 14

የሕዝቡ ማመፅ

1በዚያች ሌሊት ማኅበረ ሰቡ ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸና አለቀሰ። 2እስራኤላውያን በሙሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ እንዲህ አሏቸው፤ “ምነው በግብፅ ወይም በዚህ ምድረ በዳ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! 3እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደዚች ምድር የሚያመጣን ለምንድን ነው? በሰይፍ እንድንወድቅ ነውን? ሚስቶቻችንና ልጆቻችንም ይማረካሉ፤ ታዲያ ወደ ግብፅ መመለሱ አይሻለንም?” 4እርስ በርሳቸውም፣ “አለቃ መርጠን ወደ ግብፅ እንመለስ” ተባባሉ።

5ከዚያም ሙሴና አሮን እዚያ በተሰበሰቡት በመላው እስራኤላውያን ማኅበር ፊት በግንባራቸው ተደፉ። 6ምድሪቱን ከሰለሏት መካከል የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዩፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ 7ለመላው የእስራኤል ማኅበርም እንዲህ አሉ፤ “ዞረን ያየናትና የሰለልናት ምድር እጅግ ሲበዛ መልካም ናት። 8እግዚአብሔር (ያህዌ) በእኛ ደስ ከተሰኘብን ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደዚያች ምድር መርቶ ያገባናል፤ ለእኛም ይሰጠናል። 9ብቻ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ እንጐርሳቸዋለንና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሯቸው። ጥላቸው ተገፏል፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከእኛ ጋር ነውና አትፍሯቸው።”

10መላው ማኅበር ግን በድንጋይ ሊወግሯቸው ተነጋገሩ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር በመገናኛው ድንኳን ለእስራኤላውያን ሁሉ ተገለጠ። 11እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? እነዚህን ሁሉ ታምራት በመካከሉ እያደረግሁ የማያምንብኝስ እስከ መቼ ነው? 12በቸነፈር እመታዋለሁ፤ እደመስሰዋለሁም፤ አንተን ግን ብርቱና ታላቅ ለሆነ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”

13ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ነገሩን ግብፃውያን ቢሰሙትስ! ይህን ሕዝብ በኀይልህ ከመካከላቸው አውጥተኸዋልና፤ 14የተደረገውንም በዚች ምድር ለሚኖሩት ሰዎች ይነግሯቸዋል። እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፣ አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋር መሆንህን፣ ደግሞም አንተ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ፊት ለፊት እንደ ታየህና ደመናህ በላያቸው እንደ ሆነ፣ አንተም ቀን በደመና ዐምድ ሌሊትም በእሳት ዐምድ እፊት እፊታቸው እየሄድህ እንደ መራሃቸው ቀድሞውኑ ሰምተዋል። 15ታዲያ ይህን ሁሉ ሕዝብ በአንድ ጊዜ ብትፈጀው ዝናህን የሰሙ ሕዝቦች፣ 16እግዚአብሔር (ያህዌ) ለዚህ ሕዝብ ይሰጠው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደ ገባለት ምድር ሊያስገባው ባለመቻሉ በምድረ በዳ ፈጀው’ ይሉሃል።

17“አሁንም እንዲህ ስትል በተናገርኸው መሠረት የጌታ ኀይል ይገለጥ፤ 18እግዚአብሔር (ያህዌ) ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩ የበዛ፣ ኀጢአትንና ዐመፃን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ የማይተው፣ ስለ አባቶቻቸውም ኀጢአት ልጆችን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ የሚቀጣ ነው።’ 19ከግብፅ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው ሁሉ እንደ ፍቅርህ ታላቅነት መጠን እባክህ አሁንም የዚህን ሕዝብ ኀጢአት ይቅር በል።”

20 እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “በጠየቅኸው መሠረት ይቅር ብያቸዋለሁ፤ 21ይሁን እንጂ ሕያው እንደ መሆኔና የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ምድርን ሁሉ የሞላ እንደ መሆኑ መጠን፣ 22ክብሬን ደግሞም በግብፅና በምድረ በዳ ያደረግኋቸውን ታምራት አይተው ካልታዘዙኝና ዐሥር ጊዜ ከተፈታተኑኝ ሰዎች አንዳቸውም፣ 23ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም። የናቀኝ ማንኛውም ሰው ፈጽሞ አያያትም፤ 24አገልጋዬ ካሌብ ግን የተለየ መንፈስ ስላለውና በፍጹም ልቡ የተከተለኝ በመሆኑ ሄዶባት ወደ ነበረችው ምድር አስገባዋለሁ፤ ዘሮቹም ይወርሷታል። 25አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በሸለቆው የሚኖሩ ስለሆነ በነገው ዕለት ተመልሳችሁ በቀይ ባሕር
በዕብራይስጥ ትርጕሙ ያም ሱፍ የሚል ሲሆን የሸንበቆ ባሕር ማለት ነው።
መንገድ ወደ ምድረ በዳው ሂዱ።”

26 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 27“ይህ ክፉ ማኅበረ ሰብ በእኔ ላይ የሚያጕረመርመው እስከ መቼ ነው? የእነዚህን ነጭናጮች እስራኤላውያን ማጕረምረም ሰምቻለሁ። 28ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ ይላል፤ እኔ ሕያው ነኝ፤ ስትናገሩ የሰማኋችሁን እነዚያን ነገሮች አደርግባችኋለሁ፤ 29በተደረገው ቈጠራ መሠረት፣ ሃያ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆናችሁና በእኔም ላይ ያጕረመረማችሁ ሁሉ በድናችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃል። 30መኖሪያችሁ እንድትሆን በጽኑ ወደ ማልሁላችሁ ምድር ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በስተቀር ከእናንተ አንዳችሁም አትገቡባትም። 31ይማረካሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን ግን አገባቸዋለሁ፤ እናንተ የናቃችኋትን ምድር እነርሱ ይደሰቱባታል። 32እናንተ ግን፣ በድናችሁ በዚሁ ምድረ በዳ ወድቆ ይቀራል። 33ካለማመናችሁ የተነሣ ከእናንተ የመጨረሻው በድን እዚሁ ምድረ በዳ እስኪወድቅ ድረስ፣ ልጆቻችሁ መከራ እየበሉ አርባ ዓመት እረኞች ይሆናሉ። 34ምድሪቱን ለመሰለል በቈያችሁበት አርባ ቀን ልክ እያንዳንዱ ዓመት እንደ አንድ ዕለት ተቈጥሮ ስለ ኀጢአታችሁ አርባ ዓመት መከራ ትቀበላላችሁ፤ ምን ያህል በእናንተ ላይ እንደ ተነሣሁም ታውቃላችሁ። 35እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህን ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም አንድ ሆኖ በተነሣብኝ በዚህ ክፉ ማኅበረ ሰብ ሁሉ ላይ እነዚህን ነገሮች አደርጋለሁ፤ መጨረሻቸው በዚሁ ምድረ በዳ ይሆናል፤ እዚሁም ይሞታሉ።’ ”

36ከዚህ በኋላ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሙሴ ልኳቸው የነበሩትና ከዚያ ተመልሰው ስለ ምድሪቱ ክፉ ወሬ በማሠራጨት ማኅበረ ሰቡ በሙሉ እንዲያጕረመርሙበት ያደረጉ፣ 37ስለ ምድሪቱም ክፉ ወሬ በማሠራጨት ተጠያቂ የሆኑት እነዚሁ ሰዎች ተቀሥፈው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሞቱ። 38ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከተላኩት ሰዎች በሕይወት የተረፉት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዩፎኒ ልጅ ካሌብ ብቻ ነበሩ።

39ሙሴም ይህን ለእስራኤላውያን ሁሉ በነገራቸው ጊዜ ክፉኛ ዐዘኑ። 40በማግሥቱም ጧት ማልደው ወደ ተራራማው አገር ወጡ፤ እንዲህም አሉ፣ “ኀጢአት ሠርተናልና እግዚአብሔር (ያህዌ) ተስፋ ወደ ሰጠን ስፍራ እንወጣለን”።

41ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ትእዛዝ ለምን ትጥሳላችሁ? ይህም አይሳካላችሁም! 42እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር ስላይደለ አትውጡ፤ በጠላቶቻችሁ ድል ትመታላችሁ፤ 43አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በዚያ ያጋጥሟችኋልና። እግዚአብሔርን (ያህዌ) ስለ ተዋችሁትና እርሱም ከእናንተ ጋር ስለማይሆን በሰይፍ ትወድቃላችሁ።”

44ሙሴም ሆነ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ታቦት ከሰፈር ሳይነሡ በስሜት ተገፋፍተው ብቻ ወደ ተራራማው አገር ወጡ። 45በዚህ ጊዜ በተራራማው አገር የሚኖሩት አማሌቃውያንና ከነዓናውያን ወርደው ወጓቸው፤ እስከ ሔርማ ድረስም አሳደዷቸው።

Copyright information for AmhNASV